“የዘንድሮው የ ኢድ-አል ፈጥር በዓል አከባበር ይለያል!!
ስታዲዮም ስደርስ የገጠመኝ የኢድ ሶላት ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የሃገር ፍቅር የተሞላ “ግድቡ የኔ ነው” የሚለው መፈክር እና ስሜት ነበር።
እንኳን ለ1442ኛው ዒድ አል ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤
ኢድ ሙባረክ!
Adanech Abiebie- አዳነች አቤቤ
የዘንድሮ የረመዳን ወር ልዩ የሚያደርገው በመላው ሃገራችን በተለይም በአዲስ አበባችን፣ ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር በመሆን በጋራ በማፍጠር ፣ አንድነትን በማሳየት ፣ በአብሮነት እሴቶቻችን ላይ እያንዣበበ የመጣውን አቧራ ለማራገፍ እና ጠላቶቻችን በዘር እና በሃይማኖት ሊከፋፍሉን ያቀዱትን ሃሳብ በመስበር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ነው።
አሁንም ፣ ወደፊትም ኢትዮጵያችንን ያሰብንላት የብልጽግና ማማ ላይ ለማድረስ ዋነኛው መንገድ፣ የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር፣ ከዚያም ከዚም የሚወረወሩብንን መሰናክሎች በመበጣጠስ መሻገር እንደሆነ መቼም ልንዘነጋው አይገባም።
በብሔርና በሐይማኖት ሊነጣጥሉን የሚፈሉጉ ሀይሎች ማወቅ ያለባቸው ፣ኢትዮጵያ ትንሽ ሲገፏት የምትወድቅ የእንቧይ ካብ አለመሆኗን ነው።
ከድህነት ለመውጣት ፈጣሪ የሰጠንን ሀብት መጠቀም መብታችን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ነውና በህዳሴ ግድባችን ሳብያ ከየትኛውም የውጭ ሃይል የሚመጣብንን ኢፍትሃዊ ጫና የማንቀበለው ከሃገራዊ ስሜት በላይ ማንንም ሳንበድል ለእውነት እና ሃገራዊ ጥቅም መቆም ሃይማኖታዊ ግዴታ እንደሆነ በመረዳት ነው።
ስለዚህ ለጥላቻ ሰባኪዎች ጆሮ ሳንሰጥ የሀይማኖት እና የህዝብ እኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን የብልጽግና ጉዞአችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል።
በተለይም ከተማችን አዲስ አበባን የጥፋት ድግስ ማእከል ለማድረድ የታቀደውን እኩይ ሴራ ተረድተን ለማምከን እያደረግን ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክረን እንድንቀጥል ላሳስብ እወዳለሁ።
ኢትዮጵያ በህዝቦችዋ ጥረት ታፍራ እና ተከብራ ብልጽግናዋን ታረጋግጣለች!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ።
ኢድ ሙባረክ!!